IIEE ResourcesPublicationsResources

ያባ እንዳወቀ ቃል!

ያኔ ነፍስ ሳላውቅ ኣንድ ኣባት ነበሩ
ረቂቅ ቃላቶች ነፍሴ ላይ የዘሩ።
ስቁነጠነጥ ውየ ቀን ካስኮላ ዎንበር
በሰንበት ቁጭ ስል ሄጀ ከእግራቸው ስር:-
“ወማይኒ ሃበ ይመርሆ የሀውር
ልጅ እንደቦይ ዉሃ በመሩት ይሄዳል
ተግተው ካላረሙት እድሜ ኣረም ይወርሳል::
ስለዚህ ልጀ ሆይ ንገረኝ ልወቀው
ምን ኣይነት ዘር ነበር ልብህ የወደቀው?”
ብለው ያዮ ነበር ነፍሴን ተጠንቅቀው።
ቃላትን በቃሌ መያዝ ባይከብደኝም
ያኔ የሚነግሩኝ ፈፅሞ ኣይገባኝም:-
“ተማሪ ቤት ዛሬ ኣዲስ ኣስተማሪ
የሰው ልጅ ኣላማ የተፈጥሮው ጥሪ
ለመሆን መቻል ነው ራስን መርማሪ!
ከሁሉ ኣስቀድመህ ራስህን እወቅ!
ራስህን እንድታውቅ ራስህን ጠይቅ!
እያለ ኣስተማረን” ብየ ስነግራቸው
እየደባበሱኝ እራሴን በጃቸው:-
“ራስን የማወቅ ምንድን ነው ሚስጢሩ?”
እያሉ ቀስ ብለው መናገር ጀመሩ።
ቃላትን በቃሌ መያዝ ባይከብደኝም
ያኔ ትርጉማቸው ፈጽሞ ኣይገባኝም።
ታዲያ በልጅ ቀልቤ ነፍስን ባላወቀ
“እኔ ምን ኣውቃለሁ እባባ እንዳወቀ?”
እላለሁ ወደውጭ ኣይኔ እያጮለቀ።
“ምንድን ነው ‘ምታየው?” ብለው ሲጠይቁ
“መድሃኔኣለም ህንጻዉ ከሁሉ ትልቁ!
እሱን ነው ያየሁት!” ብየ ስነግራቸው
እየደባበሱኝ ራሴን በጃቸው:-
“ህንፃነት ኣይደለም ታላቁ ሚስጢሩ
ፈጣሪና ፍጡር እንዲነጋገሩ
ድንጋይ ልቡን ከፍቶ ሰው በተቀበለ
እነሆ ይኖራል ድንቅ እየተባለ።
ንጉስ ክብሩን ንቆ ካፈር በወደቀ
ኣፈር ፍቅር ሆነ ጥበብ ኣፈለቀ::
ልጀ ይሄውልህ የእግዜር ድንቅ ስራ
ደሙን ዉሃ ኣድርጎ ስጋውን እንጀራ
ተካፈሉት ብሎ የሰጠን ሰውነት
በመካከላችን የተከለው ገነት
ህንፃው ላይ ታትሟል የፍቅር ኣብነት::
ጳወሎስም በመልዕክት–
‘ወተዘክሮ ሞት በኩሉ ጊዜያት” – እያለ ሲያስረዳ
‘ሞት ህንፃ ላሊበላ ኩለሄ እንግዳ ‘
ያለው ባለቅኔ እየተደነቀ
ታምር ቢያጣለት ነው ከሞት የተለቀ!”
እያሉ ሲነግሩኝ “እሽ ኣባ እንዳወቀ!”
እላለሁ ወደውጭ ኣይኔ እያጮለቀ።
ቃላትን በቃሌ መያዝ ባይከብደኝም
ያኔ የሚነግሩኝ ፈፅሞ ኣይገባኝም
አሳቸውም ቢሆን ይህንን ያውቃሉ
የሰማዩን ከምድር እያመሳሰሉ
ግዕዝ ካማርኛ እየቀላቀሉ
በእምነት ቃላቸውን መናገር ቀጠሉ
“ ‘እስመ ትሄይል እሳተ ፍቅር ዘውስተ ልቦሙ ዘኣንደዳ መድህን’
ኣለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር
ፈጣሪ በየትም በምንም ላይ ነበር።
የሱ ክብር በሱ መቅረቱን ባይወደው
ፍቅርን ሰው እንዲሆን ወዳፈር ሰደደው::
ከራሱ ወጥቶ ካፈር በወደቀ
ያምላክ ማንነቱ በሰው ልብ ፀደቀ::
ሰውም ማንነቱን ማወቅ እንዳይከብደው
ከጎኑ ኣጥንት ወስዶ ከሰው ኣዛመደው::
ከቅዠቱ ነቅቶ ሰውን በጠየቀ
ሰው ህይወት ኣገኘ ራሱን ኣወቀ!!”
ብለው ሲጨርሱ “እሽ ኣባ እንዳወቀ”
ብየ እመልሳለሁ ኣይኔ እያጮለቀ።

ቃላትን በቃሌ መያዝ ባይከብደኝም
ያኔ የሚነግሩኝ ፈፅሞ ኣይገባኝም
አሳቸውም ቢሆን ይህንን ያውቃሉ
የሰማዩን ከምድር እያመሳሰሉ
ግዕዝ ካማርኛ እየቀላቀሉ
በእምነት ቃላቸውን መናገር ቀጠሉ::

“ፍቅር ሰሃቦ ለወልድ ሃያል እም መንበሩ”
ብለው ሊቃውንቱ እንደተናገሩ
ትሁት ቅን ከሚሆን ፍቅር የተነሳ
ሰው ለማስገር ችሏል ፈጣሪን እንደዓሳ።
የዘመኑ ሰው ግን ከሰው ተነጥሎ
ልፈልግ ነው ይላል ጠፍቻለሁ ብሎ::
ሌላ ሰው ለማግኘት ከራሱ ሳይወጣ
ጠፊውን ሊፈልግ ጠፊው ከየት መጣ?
ታዋቂው ከሆነ ራሱን የሚያውቀው
የሚያውቀው ከሆነ ዞሮ ሚታወቀው
ራሱን ራሱ የት ሆኖ ጠየቀው?”
በማለት ቀጠሉ እኔም እሽ ኣልሗቸው
የሚሉት ሳይገባኝ እየሰማሗቸው::
“ልጀ ይሄውልህ ራስን ለማወቅ
ወደገጠር መውጣት ወደሰፈር መዝለቅ
ከሰው መነጋገር ከሰው መተዋወቅ ::
ራስን ለማወቅ ራስን ለማግኘት
ፍቅርን ለመዘመር ከሰው ጋር መገኘት።
ከሰው ዘንድ ነውና የሰው ልጅ ሰውነት
እኔነት ጥላ ነው ኣይሆንም ማንነት::
ያለሰው ራሴን ኣፈቅራለሁ ላለ
ፍቅር ኣይፈቀርም ሌላ ሰው ከሌለ::
ወደፍቅር ኣምባ ተግተው ለሚያቀኑ
በሰው መካከል ነው የእግዚኣብሄር ዙፋኑ።”
እያሉ ነገሩኝ እኔም ሰማሗቸው
ተቀምጨ ሳለ በሰንበት ከእግራቸው::

ዛሬ እሳቸው የሉም ሄደዋል ኣምላክ ጋ
ዘመናት ኣልፈዋል ክረምት እና በጋ
እኔም ጠፍቻለሁ ራሴን ፍለጋ:;

እኔ ለእኔ እያልሁኝ እኔ ስመናተል
እድሜየን ጨረስሁት ራሴን ስከተል
ራሴን ፍለጋ ስጏዝ በዙሪያየ
ለካስ ኣልፍ ነበር እኔ ለጥላየ……….
****************************
ለኣባ እንዳወቀ /ዘካርያስ ዋሴ/ የቅ/ላሊበላ ሰንበት ት/ቤት ተማሪ በነበርሁበት ጊዜ ለዘላለማዊ ኣባታዊ ትምህርታቸው እጅግ ትንሽ ማስታወሻ፤
በኣስተምህሮተ ቃላቸው ፍቅርን እንደእሳት ጥበብን እንደውሃ በሰው ሂወት ላይ ማፍሰስ ለሚችሉ ለእርሳቸው ­­ – እና –
ኣይተን ላላስተዋልናቸው ሰምተን ላላዳመጥናቸው ለእኛ ….

2 thoughts on “ያባ እንዳወቀ ቃል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *